PSTS

ሰሌዳን በቴክኖሎጂ…………

የተሸከርካሪ ሰሌዳን የማምረትና የማሰራጨት ኃላፊነት ከትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር በውክልና ተረክቦ ስራውን በማከናወን ላይ ያለው ፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት የሰሌዳ ማምረቻ መሳሪያዎች ከጀርመን ሀገር በማስመጣት ፍጥነትና ጥራቱን በጠበቀ መልኩ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡

ኤሪክ ኤች ኤጂ ከተባለው ታዋቂ የጀርመን ሀገር የሰሌዳ ማሽን አምራች ከሆነው ድርጅት ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ ስራ የጀመረው ማሽን በጥራትና በፍጥነቱ እንዲሁም በቴክኖሎጂ ግብአቱ የሰለጠኑት ሀገራት የሚጠቀሙበት መሆኑን የገለፁት ጀርመናዊ ባለሙያዎች እንዴት እንደሚሰራ ለፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፍሬህይወት ትልቁ፣ ለም/ዋና ዳይክተሩ ለአቶ አበባው ልየውና ለማኔጅመንት አባላቱ ገለፃ አድርገዋል፡፡

አዲስ የገባው ማሽን ቀደም ሲል አልፎ አልፎ ይታዩ የነበሩት የጥራት ችግሮች ሙሉ በሙሉ እንደሚቀርፍ የተገለፁ ሲሆን በተለይ በአመራረት ወቅት የሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች ቢሯቸው ቁጭ ብለው ቁጥጥር እንዲያደርጉ ስለሚያግዝ የሚከሰቱ የስነ ምግባር ችግሮችን በቀላሉ ለመቆጣር እንደሚያስችል ባለሙያዎቹ ለስራ ኃላፊዎች ገልፀዋል፡፡

“ማሽኑ እጅግ ዘመናዊ ከመሆኑ የተነሳ ያጋጥሙን የነበረ የተለያዩ ችግሮች በመቅረፍ ረገድ የሚኖረው እገዛ ከፍተኛ ነው” ያሉት የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር “ከቀድሞው ፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የተረከብናቸው ሰሌዳ ማምረቻ ማሽኖች አሮጌና ጊዜ ያለፈባቸው ስለነበሩ የተለያዩ የጥራት ችግሮች ያጋጥሙት ነበር፡፡ ይህ በከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ የተገዛው ሰሌዳ ማምረቻ ማሽን በጊዜ ፣በጥራትና በፍጥነት የተሻለ በመሆኑ የማምረት አቅማችንን ያሳድግልናል፡፡ በዚህም የደንበኞቻችንን ፍላጎት የበለጠ ለማርካት ተጨማሪ አቅም ይፈጥርልናል፡፡” ብለዋል፡፡

“ማሽኑ በሰዓት ከ100 – 120 ሰሌዳዎችን ማምረት እንደሚችል“ የገለፁት በኢትዮጵያ የኩባንያው ወኪል የሆነው ኦፕቲማክስ ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማ ዋና ስራ አስኪሂያጅ አቶ ውብሸት ጌታሁን ስለማሽኑ አጠቃላይ ሁኔታ ለሰራተኞች ስልጠና መሰጠቱን ገልፀዋል፡፡

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *