በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ማምረቻ ኢንዳስትሪ ያመረታቸውን ዘመናዊ ሃገር አቋራጭ አውቶብሶችን በዛሬው እለት ለፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት አስረከበ።
በእለቱም የሃገር መከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር እና የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር አብርሀም በላይ እንደተናገሩት የምርቶችን ጥራት በማሳደግ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነታችንን ማሳደግ አለብን ብለዋል።
የትራንስፖርት እና የሎጅስቲክስ ሚኒስትር ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ እንደገለፁት፤ በቀጣይ ከግሩፑ ጋር በመተባበር በኤሌክትሪክ ሀይል የሚሰሩ አውቶብሶችን በማምረት ለነዳጅ ግዥ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት በጋራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ በበኩላቸው በቀጣይ መዋቅራዊ አደረጃጀቶች በማስተካከል ለምርት ጥራትና ለገበያ ልዩ ትኩረት በመስጠት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡
ከካርበን ልቀት ነጻ የሆኑ ፣ ነዳጅን የማይጠቀሙ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን ለማምረት መታቀዱንም ዋና ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡
የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖር አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬህይወት ትልቁ በበኩላቸው አውቶብሶቹ ዘመናዊና ተሳፋሪዎችን የሚመጥኑ ተደርገው መሰራታቸውን ገልፀው በቀጣይ ከግሩፑ ጋር ሌሎች ስራዎችን እንሰራለን ብለዋል።
ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ማምረቻ ኢንዱስትሪ በዛሬው እለት ያስረከባቸው አውቶብሶች ከፍተኛ የፈረስ ጉልበት ያላቸው፣ የ45 ሰዎች መቀመጫ፣ በቂ የሆነ የእቃ መጫኛ ፣ በውስጡም የመጸዳጃ እና የማቀዝቀዣ ክፍል ያላቸው ሲሆኑ ሙሉ በሙሉ አርቴፊሻል ኢንተለጀንት ሲስተም የተገጠመላቸው ናቸው፡፡
ከታዘዙት 50 አውቶብሶች ግማሾቹ የርክክብ መርሃ ግብሩ አካል ሲሆኑል አምስቱ ደግሞ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ተደርገው የተመረቱ መሆናቸውን ከኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።