ከቢሾፍቱ፣ ከሰንዳፋ፣ከጫንጮ፣ ከሆታ፣ ከሱሉልታና ከሌሎች ከአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት ተተቃሚዎች የአውቶቡስ አስተባባሪዎች ተወካዮች ከፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት የማኔጅመንት አባላት ጋር በአገልግሎት አሰጣጡ ዙሪያ ውይት አካሄዱ፡፡
ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የአገልግሎት ዋና ዳይክተር ወ/ሮ ፍሬህይወት ትልቁ “አዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች የትራንስፖርት ተጠቃሚ ተወካዮች ዘወትር አገልግሎት አሰጣጣችን የተሳካ ይሆን ዘንድ ችግሮችን እየተከታተሉ ከማረም ባለፈ በድርጅታችንና በተጠቃሚው መካከል እንደ ድልድይ ሆነው በማገልገል እየሰጣችሁን ላለው ቅን አገልግሎት ምስጋናችን እጀግ የላቀ ነው “ብለዋል፡፡
“የሚያጋጥመንም ችግሮች እንደ አንድ ቤተሰብ በመሆን ለመፍታት ከሞከርን ከኛ አቅም በላይ የሚሆን ችግር አያጋጥመንም ፡፡ ለዚህም ነው ድርጅታችን በቀን ከመቶ ሺህ ሰራተኛ በላይ እያገለገለ የጥራትና የአይ ሶ ሰርተፊኬት ተሸላሚ የሆነው ፡፡ ላደረጋችሁት ሁሉ እጅግ በጣም እናመሰግናለን፡፡” ሲሉም አክለዋል፡፡
የኮሚቴ አባላቱ በጋራ እንደገለፁት “በአሁኑ ጊዜ ይህ የትራንስፖርት አገልግሎት ባይኖር ኖሮ አይደለም ከኦሮሚያ ከተሞች ከአዲስ አበባ እንኳን ከቤት ወደ ስራ ከስራ ወደ ቤት ተንቀሳቅሶ መስራት እጅግ ፈታኝ ነው “ ብለዋል
“ከትራንስፖርት እጦት እንግልቱ ባሻገር በአማካኝ ከቤት ወደ ስራ ከስራ ወደ ቤት ለመጓጓዝ አንድ ሰው በአንድ ቀን ከ80 እስከ 100 ብር ማውጣት ይኖርበታል፡፡ ካለው ኑሮ ውድነት አንፃር ይህን ማድረግ እጅግ ይከብድ ነበር፡፡ መንግስት ይህን ለሠራተኛው አስቦ ማድረጉ ምስጋና ይባዋል፡፡“ ያሉት ተወካዮቹ “ፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት አውቶቡሶች በጥበብ እያብቃቃ አገልግሎት ለመስጠት እያደረገ ያለውን ጥረት እጅግ ይደንቃል “ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“ይሁን እንጂ እያደር እየጨመረ በመጣው የትራንስፖርት ተጠቃሚ ሳቢያ በአውቶቡሶች ላይ መጨናነቆች አሉ በየጊዜው ቆጠራና ዳሰሳ እየተደረገ መጠነኛ ተሳፋሪዎች ካሉበት ወደ ተጨናነቀው በማዘዋወር በስራ እየተሰራ በጊዜያዊነት ችግሩን መቅረፍ ይቻላል፡፡ ቢሆንም ከሀገራዊ ችግር አንፃር ተጨማሪ አውቶቡሶች ለመግዛት ችግር እንዳለ ተረድተናል፡፡ ቢሆንም ጥረቱ መቀጠል አለበት“ ሲሉ ገልፀዋል፡፡
“የተጨማሪ አውቶቡሶች ግዢ ባጋጠመን የውጪ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ አሁን ባለው ሁኔታ አልተሳካልንም። ያለንን ውስን ሀብት በመተሳሰብና በመተዛዘን ለኔ ብቻ ሳይሆን ለኛ በማለት መጠቀም አለብን፡፡ ለዘላቂ ግን የጠየቅነው የውጪ ምንዛሪ ሲፈቀድና ሲገኝ ተጨማሪ አውቶቡሶችን አስመርተን በጥናት ወደለየናቸው መስመሮች እናስገባለን፡፡” ያሉት የድርጅቱ ዋና ዳይክተር ወ/ሮ ፍሬህይወት ትልቁ፡፡ “እንደ ድርጅቱ ተወካዮች ሆናችሁ ያለውን ሁኔታ ለትራንስፖርት ተጠቃሚዎቻችን በማስረዳት የበለጠ የተሳካ አገልግሎት እንድንሰጥ የበኩላችሁን ትወጡ ዘንድ አደራ እላለሁ፡፡” ብለዋል፡፡