ግንቦት 16 ቀን 2014 (ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር) የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ሚንስትር ክብርት ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ግርማ ዋቄና ከአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው ጋር በሚኒስቴር መ/ቤቱ ጽ/ቤት ተወያይተዋል፡፡ ውይይታቸው በአቬይሽንና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ዙሪያ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካ ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሚንስቴር መ/ቤታችን ጋር በጋራ የሚሰራቸው የሎጂስቲክስና አቬይሽን አገልግሎቶች ለሀገር ግንባታ ቁልፍ መሆናቸውን ክብርት ሚንስትር ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ገልፀዋል፡፡ የካርጎ አገልግሎት ቀልጣፋ መሆን ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንደሚሰጥ የጠቆሙት ክብርት ሚንስትር ዘመናዊ የሎጂስቲክስ ስርዓት መኖር ደግሞ ሀገራችን ለተያያዘችው ፈጣን የዕድገት ጉዞ ቁልፍ ነው ብለዋል፡፡ አየር መንገዱ ካለው ሰፊ የካርጎ አገልግሎት አንፃር ተጨማሪ የሎጂስቲክስ መሠረተ ልማት እንደሚያስፈልገው ገልፀው ይህን እውን ለማድረግ ከአየር መንገዱ ጋር እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ያደጉት ሀገራት በሎጂስቲክ መስክ ያስመዘገቡተ ስኬት ለእድገታቸው ቁልፍ መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ የአየር መንገዱ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ግርማ ዋቄ ናቸው፡፡ በተለይ የዘመነ የሎጂስቲክስ ስርዓት ያላቸው የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ቅልጥፍናን ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር አጣምረው በመስራታቸው የተረጋጋ ኢኮኖሚ መገንባት መቻላቸውን አብራርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመላው ዓለም በሚያደርገው በረራ የሎጂስቲክስ ስርዓቱን በማዘመንና ተጨማሪ የካርጎ ተርሚናሎችን በመጠቀም በአፍሪካ ምሳሌ ለመሆን እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ይህን እውን ለማድረግ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ቁልፍ አጋር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር እንደ ፖሊሲ አውጪ ተቋም የሚሰጣቸው ድጋፎች ለአየር መንገዱ አጠቃላይ አገልግሎት የማይተካ ሚና የሚጫወት መሆኑን ገልፀው በሎጂስቲክ እና አቬይሽን ዙሪያ ይበልጥ ተቀራርቦ በመስራት ያለንን ትስስር ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡************• ትራንስፖርት ለላቀና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት