ዘጠኝ የዩቶንግ ካምፓኒ የደንበኞች ልዑካን ቡድን አባላት በፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት በመገኘት የስራ ላይ የልምድ ልውውጥ አደረጉ፡፡የልዑካን ቡድኑን ተቀብለው የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የድርጅቱ የኦፕሬሽን ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ፉፋ “የምንሰራውን ስራ ለመመልከትና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ድርጅታችንን መርጣችሁ ከዙምባብዌ በመምጣታችሁ ትልቅ ክብርና ኩራት ይሰማናል” ካሉ በኋላ “በምናደርገው የጋራ ቆይታ ከእናንተም የላቀ ልምድ እንደምናገኝ ባለ ሙሉ ተስፋ ነን፡፡” ብለዋል፡፡ የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት በቢሾፍቱ ተሸከርካሪ መገጣጠሚያ በሀገር ውስጥ አስመርቶ ለትራንስፖርት አገልግሎት እያዋላችው ያሉ የዩቶንግ አውቶቡሶችን በተለይ ለፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኛው በተገቢው ሁኔታ አገልግሎት ላይ ለማዋል እየተደረገ ያለው ጥረት፣ ድርጅቱ እየሰጣቸው ስለሚገኙ ዋና ዋና አገልግሎቶች፣ ስለድርጅቱ አጠቃላይ መዋቅራዊ አደረጃጃትና የሰው ሃይል ስብጥር፣ አደጋን ተከላክቶ ስለማሽከርክር የሚደረጉ ጥንቃቄዎችን በተለይም የተሸከርካሪዎች የደህንነት አስተዳደር፤ ቅድመና ድህረ የተሸከርካሪዎች የቴክኒክ ምርመራ እና የመከላከል ጥገናን በተመለከተ ለልዑካን ቡድኑ በድርጅቱ በስራ ኃላፊዎች ሰፊ ገለፃ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም የተሽከርካሪዎችን የስምሪት አስተዳዳር ለማሻሻል ጥቅም ላይ የዋለውን ቴክኖሎጂ ኢንተለጀንሲ ትራንስፖርት ሲስተም /ITS/ ለማደራጀት የተደረገው ጥረትና የተገኘውን ውጤት አስመልቶ በጉብኝት የታገዘ ገለፃ ተደርጓል፡፡ ድርጅቱ ባሉት ውስን ተሸከርካሪዎች በቀን ከመቶ ሺህ ተጠቃሚ በላይ ለማጓጓዝ እየተከተለ ያለውን ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ዘዴ እንዲሁም የድርጅቱን አወቃቀር በተመለከተ የአገልግሎቱ የኦፕሬሽን ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል ተዘራ ለልዑካን ቡድኑ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በልምድ ልውውጡ ማጠቃለያ ላይ ንግግር ያደረጉት የልዑካን ቡድኑ ተወካይ “ባዩት የስራ እንቅቃሴ እጅግ መደሰታቸው፣ በተለይ ድርጅቱን በቴክኖሎጂ ለማዘመን እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት መደነቃቸውን ገልፀዋው በአገራችን ዝምባብዌ ልንተገብረው ለምንፈልገው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ልምድ ትክክለኛውን ድርጅት በመጎብኘታችን እድለኞች ነን” ሲሉ ገልጸዋል።