የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት የ2014 የሦስተኛ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለባለድርሻ አካላት አቅርቦ በአፈጻጸሙ ላይ ውይይትና ምክክር ተደረገበት ፡፡ከሁሉም አውቶቡሶች የትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚ ተወካይ አስተባባሪዎች ተሳታፊ የሆኑበትን የውይይት መድረክ በንግግር የከፈቱት የትራንስፖርት ኦፕሬሽን ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ፉፋ “የህዝብ ክንፍ ድርጅት አገልግሎት መሰጠት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የህዝብ ክንፍ አባላትና አስተባባሪዎች ሁሌም በሚዘጋጀው መድረክ በመገኘት የሚሰጡን አስተያየት በህዝብ ዘንድ ድርጅቱ ላገኘው ክብርና በጥራት ላገኘው ሽልማቶች የማዕዘን ራስ ስለሆነ ሁሌም በግልፅ አስተያየት ለሚሰጡን የህዝብ ክንፍ አባላቶችና አስተባባሪዎች ያለን ክብር የላቀ ነው “ብለዋል፡፡በ2014 ድርጅቱ ካቀዳቸው ዕቅዶች መካከል ለዘጠኝ ወራት ይከናወናሉ ተብለው የታቀዱ ተግባራት ቀርበው ከተሳታፊዎቹ አስተያት ተሰጥቶበታል፡፡ የውይይቱ ተሳታፊዎች በአሰራር ላይ የሚታዩ የአፈጻጸም ክፍተቶች ይስተካከሉ ዘንድ አስተያየት ሰጥተው አገልግሎት እየሰጠ ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት ለመንግስት ሰራተኛው በገንዘብ የማይለካ የሞራል ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ “የህዝብ ክንፍ አባላቶች ሁሌም ከጎናችን በመሆን የሚታዩ ክፍተቶችን እዚያው ከባስ ካፒቴኖቻን ጋር በመወያየት ለመፍታት የምታደርጉት ጥረት እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ለዚህ አኩሪ ተግባራችሁ ድርጅታችን ዕውቅና ይሰጣል፡፡” ያሉት የድርጅቱ ዋና ዳይክተር ወ/ሮ ፍሬሕይወት ትልቁ “ከዚህ በበለጠ የባለቤትነት ስሜት ህገወጥ አሰራሮችን ለመከላከል የበኩላችሁን ልትወጡ ይገባል፡፡” ሲሉ ውይይቱን አጠቃለዋል፡፡