በማወቅ፣ በመሰልጠን፣ ለህሊናና ለትራፊክ ህግ ተገዢ በመሆን ልንከላከለው በምንችለው የመንገድ ላይ የትራፊክ አደጋ በሚያደርሰው ጥፋት ብዙ ጎጆዎች ፈርሰዋል፡፡ ብዙ ቤተሰቦች ተበትነዋል፡፡ አባት እናታቸውን ያጡ ህጻናት ለችግር ተዳርገዋል፡፡ ለእነዚህ ህፃናት አለሁ ብሎ ደራሽ መሆን ፅድቁ በምድርም በሰማይም ነው፡፡ የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በዚሁ አሰቃቂ አደጋ ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናትን አስተምሮ ለወግ ለማዕረግ ሊያበቃ 5 ህፃናትን ተረክቧል፡፡ ድርጅቱን ወክለው በእናትነት ወግ ህፃናቱን የተረከቡት የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር “እነዚህ ህፃናት ልጆቻችን ናቸው፡፡ በዚህ ዕድሜ ወላጅን ማጣት ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ ሁሉም ይረዳዋል፡፡ ዛሬ የተረከብናቸውን አምስት ህፃናት ምንም እንኳን እንደወላጆቻቸው ባንሆንም ወላጆቻቸውን ተክተን በቤተሰብ ፍቅር ተንከባክበንና አስተምረን ለወግ ለማዕረግ ልናበቃቸው ቃል ገብተን ተረክበናቸዋል፡፡ ከህፃናቱ መካከል የነገ ሀገር መሪ፣ዶክተርና ኢንጂነር፣ እንደሚገኝ ተስፋ አለን፡፡ ድርጅታችን ይህን ለማድረግ በህጋዊ መልኩ ህፃናትን የተረከበው በላቀ ደስታ ነው” ብለዋል፡፡በዕለቱ በክብር እግድነት የተገኙት የትራንስፖርት ሚኒስቴር የጽ/ቤት ኃላፊና የሚንስትሯ ተወካይ አቶ ገረመው ዘለቀ “የነዚህን ህፃናት የነገ ተስፋ ለማለምለምና አለኝታ ለመሆን የተረከባቸውን የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በክብርት ሚኒስትሯ ስም ከፍተኛ ምስጋና አቀርባለሁ፡፡” ካሉ በኋላ “በተሸከርካሪ አደጋ ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናትን ከመርዳት የላቀ የሞራል ደስታ የለምና ሌሎች ተቋማትም ይህን መሰል ሰናይ ተግባር ሊከተሉ ይገባል” ብለዋል፡፡ “የመንገድ ላይ የትራፊክ አደጋ ምን ያህል አሰቃቂ መሆኑን በእነዚህ ወላጆቻቸውን ባጡ ህፃናት ለማየት ይቻላል፡፡” ያሉት ደግሞ መድህን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ጀማል አባሶኤቡ “የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት እነዚህን ህፃናት በመረከቡ ምስጋናዬ የላቀ ነው፡፡” ብለዋል፡፡